የሀዲያ ዞን አጠቃላይ ገጽታ

የሀድያ ዞን በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግሥት ውስጥ ከሚገኙ 14 ዞኖች አንዱ ሲሆን የዞኑ ቆዳ ስፋት 3,950.2ዐ ካሬ ኪ.ሜትር ነው፡፡ ዞኑ በ1ዐ ወረዳዎች በሀያ ሁለት ከተማ ቀበሌያት እና በ323 የገጠር ቀበሌዎች የተደራጀ ነው፡፡ ዞኑን በሰሜን ጉራጌ ዞን፣ በሰሜን ምስራቅ ስልጤ ዞን በምስራቅ ሀላባ ልዩ ወረዳ፣ በሰሜን ምዕራብ የም ልዩ ወረዳ፣ በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና ደቡብና ደቡብ ምስራቅ ካምባታ ጠምባሮ ዞን ያወስኑታል፡፡ የዞኑ አቀማመጥ ሜዳ የበዛበት ኘላቶማ ሆኖ በተለይ በሥራ ሥር፣ በበቆሎ፣ በስንዴ፣ በእንሰትና በጤፍ እንዲሁም በቀንድ ከብት እርባታ የታወቀ ነው፡፡ የዞኑ ርዕሰ ከተማ ሆሣዕና ከክልሉ ዋና ከተማ ከሀዋሳ በ2ዐ5 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ በ1999 ዓ/ም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት መሠረት የዞኑ አጠቃላይ የሕዝቡ ብዛት 1,243,776 ሲሆን ፋ/ኢ/ል/ ቢሮ 2007 ፕሮጄክሽን ወንድ 777,690 ሴት 785,751 ድምር 1,563,441 እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ከዚህ ዉስጥ 1,368,399 በገጠር እና 195,042 በከተማ የሚኖር ነዉ፡፡
በዞኑ በርካታ የመሠረተ ልማት አውታሮችና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተሠርተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ በትምህርት ዘርፍ 75 መዋዕለ ህጻናት፣ የአንደኛ ደረጃ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ሳይክል 483 ት/ቤቶች፤ በሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ሳይክል 65 ት/ቤቶች፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ 1 እንዲሁም 1 ዩኒቨርሲቲ፣ 1 የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ፣ 1 የመንግሥት የጤና ሳይንስ ኮሌጆች፣ ጤናን በተመለከተ 310 የጤና ኬላ፣ 61 ጤና ጣቢያ እና 1 የመንግሥት ሆስፒታል ይገኛሉ፡፡
መሠረተ ልማትን በተመለከተ በመንገድ ዘርፍ 1185.53 ኪ.ሜ ጥርጊያ፣ 152 ኪ.ሜ ጠጠር እና 65.4 ኪ.ሜ የአስፋልት መንገድ፣ የቀበሌ ተደራሽ መንገዶች (UURAP) 147.53 ኪ.ሜ እና ኮብል ስቶን መንገድ 4.947 ኪ.ሜ ተዘርግቶለታል፡፡ ስልክን በተመለከተ 908,263 የሞባይል መስመሮችና 7,354 ባለሽቦ የመስመር ስልኮች ተዘርግተዉ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ 26 ፖስታ ቤቶች እና ወኪል ፖስታ ቤቶች በዞኑ ሲኖሩ፣ በሁሉም ወረዳዎች ዉስጥ የሚያገኙ 13 ከተሞችም የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ የውሃ አገልግሎትን በተመለከተ 200 የጐለበቱ ምንጮች፣ 324 የተቆፈሩ ጥልቅ ጉድጓዶች፣ 360 የተቆፈሩ ጥልቀት የሌላቸዉ ገድጓዶች እና 1 የተቆፈረ ግድብ መኖሩን መረጃዎች ያሳያል፡፡

በሀዲያ ዞን በርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ መስህቦች ይገኛሉ፡፡ ከተፈጥሮአዊ መስህቦች፣/መካከል ፍል ውኃዎች /የሀዎራ ጠበል/ ፏፏቴዎች የገሙና፣የጐንቦራ፣ የሀብቾ፣የብላቴ/ሐይቅ/፣ ቦዬ ሐይቅ ሠንሠለታማ ተራሮች/ሸንቆላ፣ቱላካላለም/ እና ተፈጥሮአዊ ገጽታዎች ለአብነት ሲጠቀሱ ከሰው ሠራሽ መስህቦች ታሪካዊነት ያላቸው ዋሻዎች /በንዳልቾ ኡልዳ፣ ባቴና ከራራ፣ሲቢያ፣ጋጋኖ/ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት /የጊቤ፣የመስመስ ቅ/ገብርኤል/ ባህላዊና የወግ ዕቃዎች የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ሆነው የውጭ አገር ዜጎች ጭምር እየጎበኙአቸው ይገኛሉ፡፡