የሀላባ ልዩ ወረዳ አጠቃላይ ገጽታ

የሀላባ ልዩ ወረዳ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ከሚገኙት 4 ልዩ ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን የልዩ ወረዳው ዋና ከተማ “ቁሊቶ” ከሀዋሳ በ85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ቁሊቶ ማለት “ናፈቀኝ” ማለት እንደሆነ ከብሔረሰቡ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ልዩ ወረዳው በክልሉ የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ በ1993 ዓ.ም. በልዩ ወረዳነት ከመዋቅሩ በፊት በ1983 ዓ.ም. የደርግን ውድቀት ተከትሎ በተከሠተው የአስተዳደር መዋቅር ለውጥ ሳቢያ በከንባታ አላባና ጠምባሮ ዞን ሥር ከተዋቀሩት አምስት ወረዳዎች አንዱ እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በ1999 ዓ/ም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት መሠረት የልዩ ወረዳው አጠቃላይ ሕዝብ ብዛት 232,241 ሲሆን ፋ/ኢ/ል/ ቢሮ 2007 ፕሮጄክሽን ወንድ 149,190 ሴት 146,156 ድምር 295,346 እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ከዚህ ዉስጥ 256,252 በገጠር እና 39,094 በከተማ የሚኖር ነዉ፡፡
ልዩ ወረዳው በሰሜን ከሥልጤ፣ በደቡብ ከሀዲያ፣ በምዕራብ ከከምባታ ጠምባሮ ዞኖችና በምሥራቅ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ይዋሰናል፡፡ አጠቃላይ የቆዳ ስፋቱ 855 ስኩዌር ኪ.ሜ ነው፡፡ መልከአ ምድራዊ አቀማመጡ 7ዐ% ሜዳማ ፣ 27% ተዳፋት 3% ተራራማ ሲሆን የአየር ንብረቱም ከ8ዐ% ወይና ደጋ ቀሪው ደግሞ ቆላማ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በልዩ ወረዳው በስፋት ከሚመረተው በርበሬ በተጨማሪ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ገብስና ስንዴ ይመረታል፡፡ በልዩ ወረዳው በርካታ የመሠረተ ልማት አውታሮችና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ በመሠረተ ልማት ረገድ መንገድን በተመለከተ የልዩ ወረዳውን የገጠር ቀበሌዎች ከቁሊቶ ጋር ለማገናኘት 495.5 ኪሎ ሜትር ጥርጊያና 224 ሜትር ጠጠር መንገድና 30 ኪ. ሜ አስፋልት ተዘርግቶለታል፡፡ በስልክ ረገድ 195417 የሞባይል መስመሮች አቅም፣1380 ቀጥታ ስልክ መስመሮች፣79 ቀበሌያት ሽቦ አልባና የልዩ ወረዳው ማዕከል ደግሞ የዲጂታል ስልክ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ረገድም 16 መዋዕለ ህፃናት፣ 103 አንደኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል እና ሁለተኛ ሳይክል የተገነቡ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ የመንግሥት፣ 93፣ 10 የግል፣ 7 ሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያና ሁለተኛ ሳይክል እና 1 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተሠርተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ እንዲሁም 79 የጤና ኬላዎች፣ 9 ጤና ጣቢያዎች፣ 2 የመንግሥት ሆስፒታል፣ 6 የግል መድኃኒት መደብር የሕዝቡን የጤና ችግር በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡

የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሆኑ 3 ከተሞችና 13 የገጠር ቀበሌዎች ሲሆኑ በንፁህ ውሃ አጠቃቀም ረገድ 43 የዉሀ ተቋማት ተሰርተዉ ህብረተሰቡ የንጹህ ዉሀ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡በልዩ ወረዳዉ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች መካከል፡- የአርሾ ፍልውኃ፣ የብላቴ ጣጤ ፏፏቴ፣ በውስጡ 11 የተለያዩ ዋሻዎችን የያዘ ስፋሜ ዋሻ፣ የብሔረሰቡ አለባበስ አጋጌጥና ባህላዊ ሥርዓቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡የሀላባ ብሔረሰብ ሀላባ የተሰኘው የብሔረሰቡ መጠሪያ ከሄላዌ ኮረብታ (ባሌ ውስጥ የሚገኝ) የተወረሰ ስለመሆኑ የተለያዩ ፅሑፎችና የብሔረሰቡ ትውፊቶች ያመለክታሉ፡፡ የብሔረሰቡ አባላት በአሁኑ ጊዜ በዋናነት ከሚኖርበት የሀላባ ልዩ ወረዳ ውጪ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ፣ በጅማ፣በባሌ እንዲሁም በደቡብ ክልል በጉራጌ፣ በካምባታ ጣምባሮ፣በሀዲያ፣ ስልጤና ሲዳማ ዞኖች በርከት ብሎ እንደሚኖር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡


ቋንቋ


የሀላባ ብሔረሰብ ቋንቋ ሀላቢሣ ከኩሽቲክ ቋንቋ ቤተሰብ ይመደባል፡፡ ሀላቢሣ ከደጋማው የምስራቅ ኩሻዊ (High land east Cushitic) ቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ከቀቤንኛ፣ ሲዳሙ አፎ፣ ካምባትሣ፣ ጣምባርሣና ሃዲይኛ ጋር የመመሳሰል ባህሪይ አለው፡፡ ለዚህም ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች የሚሰጡት ምክንያት ታሪካዊ አመጣጣቸው ከአንድ አካባቢ መሆኑና አሁንም አጐራባቾች ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ቋንቋውን ለማሳደግ የተወሰኑ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ለአብነትም አንግሊዝኛ-አላብኛ መዝገበ-ቃላት እና “የጀርመንና-አንግሊዝኛ-ሀላብሳ መዝገበ- ቃላት”፣የሀላብሣ ቋንቋን የትምህርት መስጫ ቋንቋ ለማድረግ የሚረዳ አጋዥ መጽሐፍ (Halabisa Grammer, phonoilogy, Morphology and Syntax) በብሔረሰቦች ም/ቤት ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በተጨማሪም በቋንቋው በአንደኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ በብሔረሰቡ ከአፍ መፍቻ ቋንቋው በተጨማሪ አማርኛ፣ ስልጢኛ፣ ኦሮምኛ፣ ከምብትሣና ሀዲይኛ ቋንቋዎች በሰፊው የሚነገሩ ናቸው፡፡


የብሔረሰቡ ታሪካዊ አመጣጥ


ሀላባዎች ከአረቢያ በመነሣት ቀይ ባህርን አቋርጠው በዘይላ በኩል ምስራቅ ኢትዮጵያ ገብተው ለ7ዐ ዓመታት ያህል በዚያው ሰፍረው ከቆዩ በኋላ ከነባር ነዋሪዎች ጋር ባለመስማማታቸው የሰፈሩበትን አካባቢ ለቀው ወደ አርሲ እንደገቡ የተለያዩ ፀሐፍት የራሳቸው መላምት አሏቸው፡፡ ኘሮፌሰር ታደሰ ታምራት በ1979 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፋቸው በገፅ 126 ላይ “የአላባና ቀቤና” /አላባ ቀቤና ገራድ/ ጥንታዊ ዝርያቸው ከሴም ዝርያ ከሆኑ ከደቡብ አረቢያ በመነሣት የዘይላን ወደብ በማቋረጥ ወደ ሐረር በመንቀሳቀስ ከ3ዐዐ-1ዐዐዐ ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሐረር አካባቢ እንደሰፈሩ ይጠቅሳሉ፡፡ከላይ የተገለጸዉን ሃሳብ የሀላባ አዛውንቶች የሚስማሙበት ሆኖ ሀላባዎች ከአረቢያ ከመጡ በኋላ ወደ አረብ ሀገር በንግድ ሥራ እየተንቀሳቀሱ ለረጅም ዓመታት የኖሩ ቢሆንም በምሥራቅ ኢትዮጵያ /ሐረር/ አካባቢ በተከሰቱ ጦርነቶች ሳቢያ ቦታውን በመልቀቅ ወደ ተራራማ አካባቢ አዲስ ኑሮ እየመሠረቱ ቀስ በቀስ ወደ ምዕራብና ደቡብ አቅጣጫ በመንቀሳቀስ በሲዳማ አካባቢ ልዩ ስሙ “ጉጉማ” የሚባል ቦታን አቋርጠው ወደ ዛሬው አርሲ፣ ባሌና ሲዳማ አዋሣኝ ደጋማ መሬት ላይ ሠፍረው እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ሀላባዎች ከሐረር ተነስተው አሁን የሚገኙበት አካባቢ በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን እስከሠፈሩ ድረስ ሦስት ትውልድ አንዳለፉ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የሀላባ ብሔረሰብ የራሱን ክብርና የአገሩን ነፃነት ለማስጠበቅ አያሌ ተጋድሎዎችን አካሂዷል፡፡ የብሔረሰቡ ትውፊቶች ሀላባዎች ከሌሎች ሕዝቦች ዘግይተው አንደመስፈራቸው በአካባቢው ከነበሩ ሌሎች ሕዝቦች ጋር ግጭቶች እንደነበሩ ያወሣሉ፡፡
በሌላ በኩል የምኒልክ ተስፋፊዎች በአካባቢው ያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ ለመግታት በጐሣ መሪዎቻቸው አማካይነት በመደራጀት ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል፣ መስዋዕትነትም ከፍለዋል፡፡ በሌላም በኩል ሥርዓቶች በተለወጡ ቁጥር ባህላቸውን ከማያስተናግድ አገዛዝ ጋር ያላሰለሰ ትግል አካሂደዋል፡፡ በዚህ ትግል አያሌ የሀላባ ተወላጆች የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በሌላም በኩል የፋሽስት ጣሊያንን ወራሪ ጦር በመቃወማቸው ብዙ የሀላባ ጀግኖች ውድ ሕይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ ለነፃነታቸው ያደረጉት ተጋድሎም ተጠቃሽ ነው፡፡

ባህላዊ አስተዳዳር


ብሔረሰቡ በነባር ባህሉ የራሱ የሆነ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት አለው፡፡ ብሔረሰቡ የሚተዳደርበት ሕግ “ሴራ” ሲባል ሕዝቡም ለባህላዊ ሴራ ተገዥ ሆኖ ይመራል፡፡ ባህላዊ መተዳደሪያ ሥርዓቱ “ሴሪዳኞማት” ይባላል፡፡ ሴራው የየራሳቸው የሆነ መጠሪያ ያላቸው የሥልጣን አካላት አሉት፡፡ ብሔረሰቡን የሚያስተዳድሩት የጐሣ መሪዎች ሲሆኑ በሀገር ጉዳይና በሕልውና ላይ የመጣ ችግር ካለ ብቻ በመሰባሰብ ይፈታሉ፡፡ የዚህ የባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት ከፍተኛው አካል ጠቅላላ ጉባዔ ወይንም ሸንጐ ነው፡፡ ይህ ሸንጐ በብሔረሰቡ አጠራር “ኦጋቴ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን የመሰብሰቢያ ቦታው ጥላ ስር ነበር፡፡ የስብሰባው መሪ “ወማ” ይባላል፡፡ በወማ ስብሰባ የሚሰጥ ውሣኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡ በየጐሣው ያሉ የጐሣ መሪዎች በብሔረሰቡ አጠራር “ቦክ ሙሪቾ” በመባል ሲታወቁ ጐሣውን የሚመራው “ዳቦ ሙሪቾ” ይባላል፡፡ እነዚህ መሪዎች በኦጋቴ /ሸንጐ/ ሥር ሆነው የቤተሰቡንና የጐሣውን አስተዳደራዊ ሥራዎች የሚሠሩ ናቸው፡፡ አጠቃላይ ስብሰባ /ኦጋቴ/ ሲኖር ኦጋቴን የሚመራው የ”ሲዴ” ጐሣ ነው፡፡ ምክንያቱም በብሔረሰቡ የሲዴ ጐሣ አባላት የነብዩ መሐመድ ዝርያ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ የየጐሣዎቹ ጉባዔ የሚመራው ግን በጐሣ መሪዎቹ ነው፡፡
የጐሣ መሪነት ስልጣን በዘር ሀረግ የሚተላለፍ ሆኖ የሥልጣን እርከናቸው የሚወሰነው ግን በግርዘት ሥርዓት ቅደም ተከተላቸው መሠረት ነው፡፡ ግርዘኞች ቁስላቸው መድረቅ ሲጀምር ለስድስት ወራት በዋርካ /ግራር/ ስር ተሰብስበው ለግርዘኞቹ ስም የሚያወጡበት ባህላዊ ሥርዓት /ነቃታ/ ላይ በሚያሳልፉት ቆይታ ቤተሰብና አገርን እንዴት መምራትና ማስተዳደር እንዳለባቸው ሰፊ እውቀትና ግንዛቤ የሚያገኙበት ሥርዓት ነው፡፡ ወደ “ነቃታ” ሄዶ ሲዴ ላይ ምልክት በማድረግ ስብሰባውን የመምራት ክህሎት ያገኛል፡፡ በቀጣይም ስብሰባዉን የመምራት ኃላፊነት ይሰጠዋል፡፡
ከአጐራባች ብሔረሰቦች ጋርም ሆነ በብሔረሰቡ አባላት መካከል ለግጭት መንስዔ የሚሆኑት የግጦሽ መሬት ጥያቄ፣ በዝርፊያም ሆነ በጋብቻ ምክንያት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ናቸው፡፡ ከ በቀደምት ጊዜያትም ሆነ አሁን ከአጐራባች ብሔረሰቦች ጋር የሚፈጠረው ግጭት ከሁለቱም ወገን በተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በሰላም ይፈታል፡፡ በሀላባዎች ባህል ሌላው ብሔረሰብ እንዳይበደል ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ በብሔረሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት በዳይ ተበዳዩን እንዲክስ ይወሰንበታል፡፡ የቅጣቱ መጠን እንደ ጥፋቱ ዓይነት የሚወሰን ሆኖ ጥፋተኛው በገንዘብና በዓይነት ለተበዳዩ ኮርማና ማር እንዲክስ ይደረጋል፡፡

በብሔረሰቡ እንደ ከባድ ጥፋት የሚታየው በዳዩ የተበየነበትን የቅጣት ውሳኔ ሳያከብር የቀረ እንደሆነ ነው፡፡ በዳይ የተበየነበትን ቅጣት አልከፍልም ካለና የሽማግሌ ውሣኔ ካልተቀበለ የጐሣ መሪው ፊት ቀርቦ እንዲዳኝ ይደረጋል፡፡ የጐሣ መሪውን ውሣኔ ካልተቀበለ የመጨረሻ ቅጣት ይጣልበታል፡፡ የመጨረሻው የቅጣት ውሣኔም ከቤተሰቡና ከጐሣ እንዲገለል፣ የአካባቢው ሕዝብ በበዳዩ ደስታና ሃዘን ላይ እንዳይደርሱ፣ ቢቸገር አንዳይረዱት፣ በአጠቃላይም፣ ከጐሣውም ሆነ ከአካባቢው አንዲገለል ይደረጋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥፋትና ቅጣት የተጣለበት ሰው በጥፋቱ ተፀፅቶ በዳዩን ከካሰና ከተቀጣ በኋላ የጐሣ መሪውንና ቤተ ዘመዱን ይሁንታ ካገኘ ብቻ የመጨረሻ ዕርቅ ይሆናል፡፡
በሀላባ ብሔረሰብ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት የሴቶች የወሣኝነት ሚና የተገደበ በመሆኑ አብረው ሸንጐ አይቀመጡም፡፡ ይሁንና ግጭቶች ተፈጥረው ጉዳዩ በዕርቅ ሲፈፀም ሴቶች በምርቃት ሥርዓቱ ላይ ይሳተፋሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ያለ ሴት ምርቃት ውሣኔው አይፀናም ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ በነፍስ ግድያ የጉማ ዕርቅ /ረጋ/ ሲፈፀም ማር ረጭታ የምታስታርቀው ሴት ናት፡፡ ሴት ልጅ በደል ደርሶባት ለሸንጐ አቤቱታ ካቀረበች በአስቸኳይ ውሣኔ ተሰጥቷት እንድትካስ ይደረጋል፡፡
ለእርቅ ማር የመርጨት ዝግጅት

ባህላዊ እሴቶች


በሀላባ ብሔረሰብ ኃይማኖታዊ /መንፈሣዊ/ ሥርዓት የሚመራው በኢማሞች ነው፡፡ በአብዛኛው የብሔረሰቡ አባላት ሙስሊሞች በመሆናቸው የእስልምናን የኃይማኖት ሥርዓት ይከተላሉ፡፡
የጋብቻ ሥርዓት
ጋብቻ በሀላባ ብሔረሰብ ትልቅ ግምት ከሚሰጣቸው ባህላዊ እሴቶች አንዱ ነው፡፡ በብሔረሰቡ ሰባት ባህላዊ የጋብቻ ዓይነቶች አሉ፡፡ እነዚህም ቀጥተኛ ጋብቻ /መኢሲሶ/፣ ቀበቶ መስጠት ጋብቻ፣ /ቡሬንአሱ/፣ ማስኮብለል ጋብቻ /ሄረና/፣ ጠለፋ ጋብቻ /ጎሱ/፣ የድንገት ጋብቻ ወጋቢላሬቡታ፣ የውርስ ጋብቻ /አጋ/ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ጋብቻ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ የራሱ ሥርዓትና ሂደት አለው፡፡
የቀጥተኛ ጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓት የሚጀምረው “ወፍ ማየት” /ጩቹ ለኢ/ በሚለው ነው፡፡ የሚያገባው ወጣት ከጓደኛው ጋር ልጅቱ ቤት ይሄዳል፡፡ በመቀጠል አባቱ በህይወት ካለ ከአባቱ ጋር አባቱ በህይወት ከሌለ ከሌላ ሽማግሌ ጋር በመሆን ይሄዱና ወፍ ማየት በሚለው ሕጋዊ ሥርዓት የወደፊት እድላቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ወደ ልጅቱ ቤት በሚመላለሱበት ጊዜ በሚጠጣበትና በሚበላበት ጊዜ ከደረሱ፣ መንገድ ላይ ውኃ ቀድታ የምትመለስ ሴት ካጋጠማቸው ልጅቱ ገዳም ነች ተብሎ ስለሚታመን ሽማግሌ ይላክና ይሁንታ ሲገኝ ጥሎሽ ይሰጣል፡፡ ጥሎሹ ኒካ /ቃል ማሰሪያ/ በሚል የሙስሊምን ህግ ተከትሎ ይፈፀማል፡፡ ብዙ ውጣ ውረድ ሳይኖር አጀብ ወይም ቤተዘመድ ሳይበዛ በሚደረግ ሥርዓት የሚፀና ጋብቻ ነው፡፡ ከቤተሰብ እውቅና ውጭ ሁለቱ ተጋቢዎች ተፋቅረው ወይም ልጅቱን በማባበል ይወስድና ለቤተሰቧ ሽማግሌ ተልኮ በእርቅ የሚያልቅ ነው፡፡ የጠለፋ ጋብቻ ከቤተሰብና ከልጅቱ ፍቃድ ውጭ በማስገደድ የሚፈፀም ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች እጮኛውን ያጣ /በሌላ የተነጠቀ/ ወጣት ከእጮኛው ቤተዘመድም ይሁን ከሌላ ቤተሰብ በድንገት በመጠየቅ የሚፈፀመው ጋብቻ የድንገት ጋብቻ /ወጋ ቢላሬቡታ/ በመባል ይታወቃል፡፡
በሀላባ ብሔረሰብ ባሏ የሞተባትን ሴት የባል ወንድም ወይም ከቤተዘመድ የተፈቀደለት የሟችን ሚስት በመውረስ ማግባት የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ጋብቻ ሥርዓት ሴቷ ቤተዘመድ መርጦ ያቀረበላትን ወንድ በባልነት ከመቀበል ውጭ መቃወም አትችልም፡፡ ሌላው አንድ ሴት የወደደችውን ልጅ ቤተሰብ ቤት በድንገት ገብታ ወድጄ እዚህ ገብቻለሁና ከዚህ ቤት አታውጡኝ ብላ የቤቱን ምሶሶ በማቀፍ የምትፈፅመው ጋብቻ ነው፡፡
በሀላባ ብሔረሰብ የግርዘት ሥርዓት ከጥንት ጀምሮ በሁለቱም ፆታዎች ላይ በእኩል ይፈፀማል፡፡ በባህሉ መሠረት የልጆች የግርዘት ዕድሜ ከ8 ዓመት በላይ ሲሆን ግርዘቱ የሚፈፀመው ትዳር ከመመስረታቸው በፊት ነው፡፡ ግርዘኞች ለመገረዝ አንድ ቀን ሲቀራቸዉ የሀበሻ ኮሶ ይጠጡና የጠጡበትን ዕቃ በጭንቅላታቸው አዙረው በመስበር ሲጨፍሩ አድረው ጧት ይገረዛሉ፡፡ ቁስላቸው መድረቅ ሲጀምር ወንዶችም ሴቶችም በትልቅ ዋርካ ወይም ግራር ሥር በመሰባሰብ ከመካከላቸው በመረጡት መሪ አማካይነት ለሁሉም ስም በማውጣት ሥርዓቱ ያበቃል፡፡
ባህላዊ በዓላትና ጨዋታዎች ብሔረሰቡ በደስታ በጥጋብና በሥራ ጊዜ የሚዘወተሩ ባህላዊ ጨዋታዎች ያሉት ሲሆን የጨዋታው ዓይነት በፆታና በዕድሜ ይወሰናል፡፡ እረኞች /ሁዌ ገዶ ሁዌው/ ሲጫወቱ፣ በሴቶች ግርዘት ወቅት ወንዶች “ሆይ ሎሌ ሎሌ”ን ይጫወታሉ፣ በወጣት ወንዶች እና ሴቶች የሚዘፈኑ የሠርግ ዘፈኖች ፣ የአዝመራ ጊዜ፣ የፉከራና ለሙገሣ የሚዘፈኑ ዘፈኞቹ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከበሮና ዋሽንትም ዋነኛ የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው ናቸው፡፡
በብሔረሰቡ ዘንድ ከባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት ባልተናነሰ መልኩ የባህላዊ እምነት ሥነ-ሥርዓት ተዘውትሮ ይካሄድ እንደነበር ይነገራል፡፡ በክርስትና ኃይማኖት መስፋፋት የተነሣ እየቀረ መጥቷል እንጂ ቀደም ሲል የተወሰነው የማህበረሰቡ ክፍል የ”ቀይዳራ” /የቃልቻ/ ወይንም “ዋዕማንቾ” እምነት ተከታዮች እነደነበሩ ይነገራል፡፡ የዚህ ልማዳዊ እምነት ተከታይ የሆኑ በሙሉ “ቃይደራ” የሚባለው አንድ የተለየ ኃይል ያለው የሁሉም አምላክ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ይህም አምላካቸው የመላውን ህዝብ ህይወት በቅርበት እንደሚከታተል እና ከጠላት፣ ከረሀብ፣ ከበሽታ፣ ከእርዛት…ወዘተ እንደሚጠብቃቸው ስለሚያምኑ ያከብሩታል; ወጉንም በሚገባ ይጠብቁታል፡፡ ይህ ካልተፈፀመና ተግባራዊ ካልተደረገ ቆሌው ይቆጣል; በዚህም የተነሣ ለቅጣት ብሎ በበሽታ ወረርሽኝ የማዝመት፣ በረሀብና እርዛት የማሰቃየት፣ በአጠቃላይ የቁም ስቃይ የማሳየት ኃይል አለው ስለሚባል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ሥፍራና ግምት ይሠጠዋል፡፡ በመሆኑም የ”ቃይዳራ” እምነት ተከታዮች ከእርሻ ምርታቸውና ከሚያረቡት ከብቶቻቸው በኩሩን ለ”ቀይደራ” ይሰጣሉ፡፡ በመስቀል በዓል ጊዜም ለአባታቸው፣ አያቶቻቸው የሙት መንፈስ መስዋዕት ያቀርባሉ፡፡

የአመጋገብ እና አለባበስ ሥርዓት


በብሔረሰቡ የአመጋገብ ሥርዓት ሴት ልጅ ከወላጅ ጋር አብራ እንድትበላ ባህሉ አይፈቅድላትም፡፡ ባህላዊ አለባበስ በፆታና በዕድሜ ይወሰናል፡፡ አዛውንቶች ጋቢ፣ ቡልኮ፣ /በቅቤ የተነከረ/ ኮት፣ ተነፋነፍ ሱሪ፣ ጉፍታ አና ጥምጣም አድርገው አለንጋ ይይዛሉ፡፡ ሴቶች ከናይለን ጨርቅ የተሰፋ ቀሚስ ልዩ ልዩ ቀለምና መጠን ባላቸው ቁልፎች ልብሳቸውን ያስጌጣሉ፡፡ ወገባቸውን በመቀነት ይታጠቃሉ፡፡ የተለያየ የፀጉር አሠራርም አላቸው፡፡ ወጣቶች እጀ ጉርድ ሸሚዝና ቁምጣ ላይ የተለያዩ ቁልፎችን በማንጠልጠል ያስጌጡና ሰደርያ ደርበው በመልበስ ከሰንደዶና አክርማ የተሠራ ባርኔጣ ያደርጋሉ፡፡
ቤት አሠራር
የሀላባዎች ባህላዊ ቤት ክብ ሆኖ ጣራው ከስንደዶ ሣር ይከደናል፡፡ ቤት ሠርቶ ከድኖ ማጠናቀቅ የወንዶች ሲሆን ሴቶች ምርጊቱንና ውስጡን የመደልደል ሥራ ይሠራሉ፡፡ ሀላባዎች ከሸክላ፣ ከእንጨት፣ ከብረት፣ ከሰንደዶና አክርማ የሚሠሯቸው የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች እና የእርሻ መሣሪያዎች አሏቸው፡፡ ከአነዚህ ሌላ ከጥጥ የሚሠሩ አልባሳት፣ ከእንሰት ተዋጽኦ የሚሠሩ የመኝታ ዕቃዎች እና የተለያዩ ባህላዊ የጦር መሣሪያዎችንም ያመርታሉ፡፡
የለቅሶና የሐዘን ሥነ-ሥርዓት
በሀላባ ብሔረሰብ ጀግና ወይም የጐሣ መሪ ሲሞት ይገለገልበት የነበራቸው ዕቃዎችና አልባሳትን በመያዝ ይለቀሳል፡፡ ሴቶች በጥፍራቸው ፊታቸውን እየቧጨሩ ያለቅሳሉ፡፡ ይሁንና በሐይማኖታዊ ሥርዓት የተከለከለ በመሆኑ ቀብር ቦታ አይሄዱም፡፡