የክልሉ አጠቃላይ ገፅታ

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትን ከመሠረቱት ዘጠኙ ክልሎች አንዱ ነው፡፡ ክልሉ በሀገሪቱ ደቡብ እና ደቡባዊ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ ሆኖ፤ በደቡብ ከኬንያ፣ በደቡባዊ ምዕራብ ከደቡብ ሱዳን፣ በሰሜናዊ ምዕራብ ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልል፣ በሰሜናዊ ምዕራብ፣ ሰሜን እና ምሥራቅ አቅጣጫ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ጋር ይዋሰናል፡፡ በኢትዮጵያ ካርታ ላይ በ4ዐ43` – 8ዐ 58` ሰሜን ላቲትዩድ (ኬክሮስ) እና 34ዐ 88`– 39ዐ14` ምሥራቅ ሎንግቲዉድ (ኬንትሮስ) መካከል ይገኛል፡፡ የክልሉ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 1ዐ9,015 ስኩዌር ኪ.ሜ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት 1ዐ% እንደሚሸፍን ይገመታል፡፡ ክልሉ በ14 ዞኖች፣ በ4 ልዩ ወረዳዎች፣ በ131 ወረዳዎች እና በ22 የከተማ አስተዳደሮች የተደራጀ ነዉ፡፡ በ2007 ዓ/ም የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ መረጃ እንሚያመለክተዉ በክልሉ 313 ከተሞች እና 3742 የገጠር ቀበሌያት የሚገኙበት ሲሆን በ1999 ዓ.ም. የተደረገውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ መሠረት በማድረግ በ2007 ዓ/ም በተደረገዉ ፕሮጄክሽን መሠረት የክልሉ ሕዝብ ብዛት ወንድ 9,422,325 ሴት 9,509,061 ድምር18,931,386 እንደሚሆን ሲገመት ይህም የአገሪቱን 2ዐ% እንደሚሸፍንና ከዚህም አኃዝ 16,755,214 በገጠር እንዲሁም 2,176,172 በከተማ ይኖራል፡፡


2ዐ% ያህሉ የክልሉ ሕዝብ 1ዐ% በሚሸፍን የአገሪቱ ክፍል ላይ መኖሩ በክልሉ ከፍተኛ የመሬት ጥበትና የሕዝብ ጥግግት መኖሩን የሚያመለክት ሲሆን የሕዝብ ጥግግቱ 164 ሰዎች በአንድ ኪሎ ሜትር ካሬ ይኖራሉ፡፡ በክልሉ 56 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩ ሲሆን እነዚህም በኦሞአዊ፣ ናይሎ ሰሀራዊ፣ ኩሻዊና ሴማዊ የቋንቋ ቤተሰቦች ይመደባሉ፡፡ ከነዚህም መካከል 42.8% የኦሞአዊ፣ 37.5% ኩሻዊ፣ 16.1% የናይሎ ሰሀራዊ እና 3.6% ሴማዊ ቋንቋ ቤተሰብ ተናጋሪዎች ናቸዉ፡፡ ክልሉ የተለያዩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የሁሉም አየር ንብረት ዓይነቶች ያሉት ሲሆን 42ዐ7 ሜትር ከፍታ ካለው በጋሞ ጐፋ ዞን ከሚገኘዉ ጉጌ ተራራ እስከ 376 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ያለው በደቡብ ኦሞ ዞን ጨልባና ቱርካና ኃይቅ አካባቢ የሚገኘው የክልሉን ዝቅተኛ ቦታን የያዘ ነዉ፡፡

ክልሉ 57.4% ቆላና ከፊል በረሃ፣ 34% ወይና ደጋ፣ 8.6% በደጋ እና በዉርጭ የአየር ንብረት የተከፋፈለ ሲሆን፣ ክልሉ ለእርሻና ከብት እርባታ ምቹ የሆነና በደን የተሸፈነ ነው፡፡ የሀዋሣ፣ የአባያ፣ የጫሞ፣ የጨው ባህርና ቱርካናን የመሳሰሉ ኃይቆች፤ የኦሞ፣ የጐጀብና የብላቴ ወንዞችና የሌሎች ጅረቶች ባለቤት ሲሆን ገናሌ-ዳዋ ባሮ-አኮቦ፣ ኦሞ-ግቤ፣ በአጠቃላይ የአገሪቱን 32% የሚደርሱ ተፋሰሶችን ይጋራል፡፡ የአጆራ፣ የሎጊታና የጋቺት እና ሌሎች ፏፏቴዎች፤ የነጭ ሣር፣ ኦሞ፣ የማዜ፣ የማጐና የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርኮች የሚገኙበትና ሌሎችም ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች የሚገኙበት ክልል ነው፡፡ ከተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች መካከል ከፍተኛው የታችኛው ኦሞ፣ የኪብሽ፣ የፊጀጅ፣ የወይጦ፣ የቦሳና እና የኮንሶ የፓልዮ አንትሮፖሎጂ እና አርኪኦሎጂካል ሳይቶች፤ የጢያና ቱቱፋላ ትክል ድንጋዮች፣ የሞቼቦራጐና አክርስ ዋሻዎችን የመሳሰሉ እንዲሁም በርካታ ትክል ድንጋዮች አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶች በስፋት የሚገኙበት ክልል ነው፡፡