ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዋነኛ የምጣኔ ሀብት መሠረት ግብርና ሲሆን የእንስሳት እርባታም ጐን ለጐን ይካሄዳል፡፡ በዋናነት የሚመረቱ ምርቶችም በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ጥራጥሬ፣ ድንች፣ እንሰት፣ ፍራፍሬዎችና የቅባት ሰብሎች ሲሆኑ ጐን ለጐን ገበያ ተኮር (commercial production) የሆኑ ቡና፣ የሻይ ቅጠል፣የጐማ ተክል ወዘተ እንዲሁም ከፍራፍሬ ማንጐ፣ አኘል፣ አቦጋዶ፣ እናናስ፣ ፓፓያና ሙዝ በስፋት ይመረታሉ፡፡ ከቁም ከብቶች፣ ከወተትና ከወተት ተዋፅኦ የሚገኘው ጥቅም ተጨማሪ የምግብና የገቢ ምንጮች ናቸው፡፡ በክልሉ የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በ3 ዞኖችና በ12 ወረዳዎች በሚገኙ አርብቶ አደሮች አካባቢ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችና የተለያዩ የተቀናጀ የአርብቶ አደር አካባቢ ልማት እየተሠራ ይገኛል፡፡

የክልሉ ዋነኛ የምጣኔ ሀብት መሠረት ግብርና ይሁን እንጂ ጐን ለጐን የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ እያደገ እንደሚገኝ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በኮንስትራክሽን፣ በእንጨት፣ ብረታ ብረት እና በጨርቃጨርቅ መስክ የተደራጁ ማኀበራት ሰፊ የገበያ ዕድል እየተፈጠረላቸው ይገኛለ፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ እንተርፕራዞች ብቃት ማሳደግና በገበያ ተወዳዳሪነታቸዉን ለማሳደግ በመጀመሪዉ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የብር 2,203,366,100 የገበያ እድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ የብር 5,489,184,753 የገበያ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

በግብርናው ዘርፍ በ2ዐዐ7 ዓ.ም መረጃ መሰረት በአጠቃላይ በዋና ዋና የምግብ ሰብሎች (የአገዳ፣ የብርዕ እና ጥራጥሬ) ምርት በ2002 ዓ.ም. የተገኘዉ አጠቃላይ ምርት መጠን 16.74 ሚሊዮን ኩንታል ከነበረበት በ2007 ዓ.ም የሰብል ዘመን 34.18 ሚሊዪን ኩንታል የደረሰ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የቡና ልማትን በተመለከተ በ2002 ዓ.ም 371,218 ሄክታር የነበረዉን የቡና ማሳ ወደ 688,000 ሄክታር ማድረስ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ በተያዘዉ እቅድ በአንድ ሄክታር 8.5 ኩንታል ለማምረት ተችሎ በአጠቃላይ 313,003 ቶን ምርት ማምረት ተችሏል፡፡ የሰሊጥ ልማትን በተመለከተ በመነሻ አመቱ 10,124 ኩንታል ይመረት ከነበረበት በ2007 ዓ.ም 100,000 ኩንታል ማምረት ተችሏል፡፡ የአትክልት ልማትን በሚመለከት በ2002 ዓ.ም 29,265 ሄክታር ከነበረበት በ2007 ዓ.ም ወደ 66,133 ሄክታር የደረሰ ሲሆን ምርታማነቱን ከነበረበት 104 ኩንታል በሄክታር ከነበረበት ወደ 133 ኩንታል በሄክታር ማድረስ ተችሏል፡፡ በቅመማቅመም ልማት በ2002 ዓ.ም 47,222 ሄክታር መሬት ከሚለማበት በ2007 ዓ.ም 67,453 ሄክታር መሬት እንዲለማ ተደርጓል፡፡ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና አጠቃቀም ረገድ የክልሉን የደን ሽፋን ከነበረበት 11.5% ወደ 19% ለማድረስ ተችሏል፡፡ የእንስሳት እርባታን በተመለከተ የቀንድ ከብት 10,421,589፣በግ 3,835,302፣ ፍየል 3,525,722፣ ዶሮ 7,741,105 ፣ አህያ 548,305 ጠቅላላ ድምር 26,532,011 ይሆናል፡፡

ኢንቨስትመንትን በተመለከተ በመጀመሪያዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ለ1257 እንቨስትመንት ፍቃድ የተሰጠ ሲሆን ከዚህም 9.864 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ መሠረተ ልማትን በተመለከተ በ2007 በጀት ዓመት የቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታን ጨምሮ በክልሉ የመንገድ ሽፋን 24,919.5 ኪ.ሜትር የደረሰ ሲሆን ከዚህም ዉስጥ 2,070 ኪ.ሜትር አስፋልት፣ 8,347.6 ኪ.ሜትር ጠጠር የለበሰ መንገድ፣ 14,763.7 ኪ. ሜትር የበጋ መንገዶች (ጥርጊያ መንገዶች) እና በቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታ ፕሮግራም (URRAP) ደግሞ 4,020 ኪ.ሜትር ጠጠር የለበሰ መንገድ ተዘርግቷል፡፡ የንጹህ ዉሃ አቅርቦትን በሚመለከት በ2007 ዓ.ም በአጠቃላይ 6,364 ተቋማት ተገንብተዉ በገጠር 5,491,821 ህዝብ፣ በከተማ 1,065,977 ህዝብ በጠቅላላዉ 6,557,798 ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ኤሌክትሪክን በተመለከተ 178 የሚደርሱ ከተሞች እና 575 የገጠር ቀበሌያት የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ስልክን በተመለከተ ለገጠር አርሶአደር ተደራሽ ለማድረግ 3,434 የገጠር ሽቦ አልባ ስልኮች ተደራሽ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

የፖስታ አገልግሎትን በተመለከተ በክልሉ 239 ከተሞች የፖስታ ቤቶችና ቅርንጫፍ ፖስታ ቤቶች እንዲሁም ወኪል ፖስታ ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን እንዲሁም፤ ሬዲዮን በተመለከተ የክልሉ FM-100.9 ሬዲዮና በሊንክ የሚገናኙ 8 ቅርንጫፍ የአካባቢ ራዲዮ ጣቢያዎች በተለያዩ ቋንቋዎች የስርጭት አገልግሎት በመስጠት ላይ ያገኛሉ፡፡ ቴሊቪዥንን በተመለከተ ከዋናው ጣቢያ ከሚተላለፍ ኘሮግራሞች በተጨማሪ የደቡብ ቴሌቪዥን ቋሚ የሳትላይት ኘሮግራም አለው፡፡ ጋዜጦችን በተመለከተ "የደቡብ ንጋት" እና "አብዮታዊ ዲሞክራሲ" ጋዜጦች፣ እንዲሁም በክልል ሴክተር መ/ቤቶች፣ በዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የሚታተሙ የተለያዩ መፅሄቶች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች 42 የማህበረሰብ መረጃ ማዕከላት እና በሁሉም የዞን ከተሞች የቪድዮ ኮንፍረንስ አገልግሎት የሚሰጡ 148 ጣቢያዎች ተዘርግተዉ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡